መስከረም 1 ቀን 2015 (ኢዜአ)ኢትዮጵያዊያን በአዲሱ ዓመት አድነታቸውን ይበልጥ በማጠናከርና የሚያጋጥሙ ፈተናዎችን በማለፍ የአገሪቱን ተስፋዎች እውን ማድረግ ይገባል ሲሉ በቻይና የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ተሾመ ቶጋ ገለጹ።
የ2015 ዓ.ም አዲስ ዓመት መባቻ እንዲሁም የአንድነት ቀን፤ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን እንዲሁም የኢትዮጵያ ወዳጆች በተገኙበት በቻይና ቤጂንግ በሚገኘው የኢትዮጵያን ኤምባሲ በድምቀት ተከብሯል።
አምባሳደር ተሾመ ቶጋ በዚሁ ጊዜ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ኢትዮጵያዊያን በአዲሱ ዓመት አድነታቸውን ይበልጥ በማጠናከርና የሚያጋጥሙ ፈተናዎችን በጽናት ማለፍ ይገባል ብለዋል።
“የአገራችን ታሪክ የጽናት ታሪክ ነው፤ ታሪካችን ለአንድም ጊዜ በአንድነታቸን ተደራድረን የማናውቅ ህዝቦች ነን፤ አንድ ሆነን ፈተናዎችን እያለፍን የኢትዮጵያን ተስፋዎች እውን እናድርግ” ሲሉም ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
ኢትዮጵያ በታሪኳ ከውጭ የተቃጡባትን ወረራዎች እየመከተች የኖረችና የመልካም ጉርብትና ተምሳሌት አገር መሆኗን አይካድም ያሉት አምባሳደሩ አሁን ላይ አገሪቱ የተቃጣባትን ችግሮች በጋራ መመከት ይገባል ብለዋል።
በተለይም መንግሥት በአሸባሪው የሕወሃት ቡድን ላይ እየወሰደ ያለውን እርምጃ ውጤታማ ለማድረግ ሁሉም ዜጋ በሃላፊነት ስሜት ለአገሪቱ ጥምር የጸጥታ ሃይሎች እንደከዚህ ቀደሙ የበኩሉን ድጋፍ ማድረግ እንዳለበት አሳስበዋል።
የጠላቶቻችን እኩይ ሴራ ወታደራዊ ብቻ ሳይሆን ኢኮኖሚያዊ ገጽታ ያለውና ላቅ ሲልም የአገሪቱን ስም የማጠልሸት እኩይ ተልዕኮም ያለው መሆኑን በመገንዘብ በጽኑ መታገል ይገባል ሲሉ አምባሳደሩ ገልጸዋል።
“ያለችን አንድ አገር ናት”፤ የአገራችን ጉዳይ ያሳስበናል፣ ይመለከተናል፣ ያገባናል በሚል መንፈስ መንቀሳቀስ እንደሚገባም ጠይቀዋል።
አዲሱ ዓመት በአዲስ አስተሳሰብ በመቃኘት በአገሪቱ ሰላም ሰፍኖ አገሪቱ የጀመረችው የአገር ግንባታ ሥራ ፍሬ የሚያፈራበትና አዲስ ድል የሚመዘገብበት ዓመት እንዲሆን ምኞታቸውን ተናግረዋል።
በቻይና የኢትዮጰያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ማኅበር ሊቀመንበር አቶ አስቻለው በላይ በበኩላቸው፤ “እኛ ኢትዮጵያዊያን አገር አደጋ ላይ ስትወድቅ በጋራ መቆምና ፈተናዎችን በጽናት ማለፍ ልማዳችን ነው”።
በአገርና በህዝብ ላይ የተቃጣን አደጋ ለመመከት ኢትዮጵያውያን የግልና የቡድን ፍላጎቶች በይደር በመተው ለመሰዋዕትነት በመሽቀዳደም አገርን ከተለያዩ ፈተናዎች አድነዋል፤ ይህም ትውልድ ከዚህ ታሪክ መማር አለበት ብለዋል።
“እኛ በቻይና የምንገኝ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያንም ከመቼውም ጊዜ በላይ በመሰባሰብና በመደራጅት አንድነታችንን በማጠናከር እርስ በእርስ በመተጋገዝ ለአገራችንና ለወገናችን አስፈላጊውን አስተዋፅዖ በማድረግ ላይ እንገኛለን” ሲሉ ተናግረዋል።
በቀጣይም በቻይና የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ለአገራቸው የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠው አዲሱ ዓመት አገሪቱ ወደተሻለ ከፍታ እንድትሸጋገር በጋራ መሥራት እንደሚገባ አሳስበዋል።
በመርሃ ግብሩ በጦርነቱ ህይወታቸውን ላጡ ሰዎች የህሊና ጸሎትና በዚሁ ጦርነት ሳቢያ ችግር ላይ የወደቁ ዜጎችን መልሶ ለሟቋቋም የሚያግዝ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብርም ተካሂዷል።