የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲና የቻይና ዥያንግ ፖሊስ ኮሌጅ በትብብር ለመስራት ተፈራረሙ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ከቻይና ዥያንግ ፖሊስ ኮሌጅ ጋር በትብብር ለመስራት የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርሟል፡፡
የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ራዕዩንና ተልዕኮውን ከግብ ለማድረስ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር ከሚገኙ የፖሊስ ተቋማት ጋር በትብብር እየሰራ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ም/ኮሚሽነር ጀነራል መስፍን አበበ÷ኢትዮጵያ እና ቻይና ለበርካታ ዓመታት በተለያ ዘርፎች በትብብር እየሰሩ መሆኑን አንስተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲም የሀገራቱን ግንኙነት ይበልጥ በማጠናከር የጋራ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ እንደሚሰራ አንስተዋል፡፡
ስምምነቱ ችግር ፈቺ ጥናትና ምርምር፣ ፖሊሳዊ ዲስፕሊንን ይበልጥ ለማሳደግ የሚያግዙ ኮርሶችን በጋራ ለማዘጋጀት፣ የተለያዩ ስልጠናዎችንና የትምህርት ዕድሎችን ለማመቻቸት እንደሚያስችል ተጠቁሟል፡፡
የትራፊክ አደጋን ሊቀንሱ የሚችሉ የወንጀል መከላከል እና የምርመራ ሥራዎችን ለማከናወን እና በቴክኖሎጂ ሽግግር በትብብር መስራት እንደሚያስችል መገለጹንም የፌዴራል ፖሊስ መረጃ ያመላክታል፡፡